የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ የሚሆንበት መንገድ ተዘግቶ መቀመጥ እንደሌለበት የሕወሓት ነባር ታጋይና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሥዩም መስፍን አሳሰቡ፡፡
አቶ ሥዩም ኢሕአዴግ ውህድ ፓርቲ ሊሆን እንደሚገባ የተናገሩት፣ ኢሕአዴግ ባህር ዳር ከተማ ባካሄደው ዘጠነኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ ነው፡፡
አቶ ሥዩም ይህንን ሐሳብ ያመጡት ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውጪ ያሉት አምስቱ አጋር ፓርቲዎች እስከመቼ ድረስ አጋር እየተባሉ ይቀጥላሉ የሚል ጥያቄ ከጉባዔው ከቀረበ በኋላ ነው፡፡
‹‹ጥያቄው ትኩረቴን ሳበው›› ካሉ በኋላ አቶ ሥዩም ለጥያቄው በቀጥታ መልስ ከመስጠት ይልቅ ትልቁን ምስል በማምጣት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡





























