አይኤምኤፍ በዓባይ ግድብ ላይ የወጣው ዘገባ የተሳሳተ ነው አለ

Nile_dam

ባለፈው ሳምንት የቡሉምበርግ የዜና አውታር የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የዓባይ ግድብ ግንባታ እንዲቀዛቀዝ የኢትዮጵያ መንግሥትን አሳሰበ በሚል ያሰራጨው ዘገባ የተሳሳተ ነው ሲል አይኤምኤፍ አስተባበለ፡፡ የአይኤምኤፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ጃን ሚከልሰን ለቡሉምበርግ በላኩት ደብዳቤ እንደገለጹት፣ ‹‹የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሙሉ ወጪው የሚሸፈነው ከአገር ውስጥ በሚገኝ ገቢ ስለሆነ፣ እኔ በማናቸውም ሁኔታ መንግሥት ይህንን የግድብ ግንባታ እንቅስቃሴ እንዲያቀዘቅዘው መጠየቅ አልችልም፡፡ ውሳኔውም ሙሉ ለሙሉ መሆን ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አይኤምኤፍ በአገሪቱ ውስጥ የሚደረጉ ማናቸውንም ፕሮጀክቶች የመገምገም ሙያዊ ብቃት የሌለው መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ለመንግሥት እንደዚህ ዓይነት ምክር አለመስጠታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

አይኤምኤፍ የአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋቱ ለአገሪቱ ዕድገት እንዲሁም በአጠቃላይ የመሠረተ ልማቱ ኢንቨስትመንት ለመቀጠሉ ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ይህን ለማረጋገጥ በአገሪቱ የታቀዱ ፈጣን ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚያስፈልጋቸው ያለውን ሥጋት ገልጿል፡፡ ‹‹ስለዚህ እነዚህ በቀጣይ ዓመታት ለታሰቡ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገው ገቢ ከአገር ውስጥ የሚገኝ ከሆነ የግል ዘርፉ ላይ ጫና ማሳደሩ አይቀሬ ስለሆነ፣ በአጠቃላይ የአገሪቷን ዕድገት ሊያቀዘቅዘው ይችላል በሚል ጥንቃቄ እንዲደረግ ብለናል፤›› ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አይኤምኤፍ የዓባይ ግንባታ እንዲቀዛቀዝ መንግሥትን ጠየቀ የሚለው ዘገባ የተሳሳተና የተዛባ ስለሆነ ብሉምበርግ ዘገባውን እንዲያርመው ጠይቋል፡፡ በአዲስ አበባ የብሉምበርግ ዘጋቢ ዊሊያም ዳቪሰን በአቋሙ እንደሚፀና ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ሪፖርተር

Comments

comments

Leave a Reply

Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>