በኢትዮጵያ የውትድርና ማዕረግ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴት ጄኔራል ተሾሙ፡፡

new_200_200

በኢትዮጵያ የውትድርና ማዕረግ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴት ጄኔራል ተሾሙ፡፡

ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ላይ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ለ34 ኮሎኔሎች የብርጋዲዬር ጄኔራልነት፣ ለሦስት ብርጋዲዬር ጄኔራሎች የሜጄር ጄኔራልነት ማዕረግ ሲሰጡ፣ ከተሿሚዎቹ መካከል የብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ ያገኙት አስካለ ብርሃኔ ተድላ የመጀመርያዋ የሴት ጄኔራል ሆነዋል፡፡

በተሿሚዎች ጄኔራሎች ዝርዝር ውስጥ ስማቸው የሰፈረው ብርጋዲዬር ጄኔራል አስካለ፣ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የሕግ አገልግሎት መምርያ ውስጥ በዳኝነትና በተለያዩ የሕግ ሥራዎች እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

በሃምሳዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኙት ብርጋዲዬር ጄኔራል አስካለ ብርሃኔ ተድላ በትግራይ ክልል በአድዋ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፣ በ1960ዎቹ መገባደጃ ለትግል በረሃ ከመሄዳቸው በፊት በአድዋ ከተማ ንግሥት ሳባ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በትግሉ ወቅት በተለያዩ የጦር ሜዳዎች ከደርግ ሥርዓት ጋር የተፋለሙት ብርጋዲዬር ጄኔራል አስካለ፣ በትግሉ ጊዜ በጦር ሜዳ የመቁሰል አደጋ አጋጥሟቸዋል፡፡ ለ17 ዓመታት ከተዋጊነት እስከ አመራር ደረጃ መሳተፋቸውም ታውቋል፡፡

ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. በድል አድራጊነት አዲስ አበባ ገብቶ መላዋን ኢትዮጵያ ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሕግ የመጀመርያ ዲግሪ የተመረቁት ብርጋዲዬር ጄኔራል አስካለ፣ አሜሪካ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ በተልዕኮ በሕግ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡

በመከላከያ ሚኒስትር የሕግ አገልግሎት መምርያ ውስጥ እያገለገሉ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር በሱዳን ዳርፉር ለሰላም አስከባሪነት ከዘመተው የኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ለስምንት ወራት ያህል መሥራታቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ብርጋዴዬር ጄኔራል አስካለ የቀድሞው ታጋይና በኋላም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩት ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት (ጆቤ) ባለቤት ሲሆኑ፣ ሁለት ሴት ልጆችም አፍርተዋል፡፡ ሜጄር ጄኔራል አበበ በ1993 ዓ.ም. በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ውስጥ በተፈጠረው ክፍፍል ምክንያት ከኢሕአዴግና ከመንግሥት አመራር መገለላቸው ይታወሳል፡፡ ሜጄር ጄኔራል አበበ በአሁኑ ወቅት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሠሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት የሴት ጄኔራል በመሆን የተሾሙት ብርጋዲዬር ጄኔራል አስካለ ብርሃኔ ተድላን ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

በኢትዮጵያ የውትድርና ማዕረጎች ታሪክ ለዚህ ከፍተኛ ማዕረግ የመጀመርያ በመሆን የተመዘገቡት ብርጋዲዬር ጄኔራል አስካለ ቢሆኑም፣ የመኮንንነት ማዕረግን ለሴት ኢትዮጵያዊያት መስጠት የተጀመረው በ1940ዎቹ በኮሪያ ዘመቻ ጊዜ መሆኑ ይነገራል፡፡ በዚያን ጊዜ ከቃኘው ሻለቃ ጦር ጋር የዘመቱ ሁለት ነርሶች የመጀመርያዎቹ መኮንኖች ሲሆኑ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሴት መኮንኖች እስከ ኮሎኔልነት ማዕረግ መድረሳቸው ይታወቃል፡፡

Comments

comments

Leave a Reply

Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>