እናቁም? ዳንኤል ክብረት

Daniel_Kibret

አንዳንዴ የትግላችን፣የጥረታችን፣የልፋታችን ውጤት መና የቀረ የሚመስልበት ጊዜ አለ፡፡ ውኃ አልቋጥር፣ ጠብ አልል ሲልብን፤ መንገዱ ሁሉ ረዥም፣ በሮቹ ሁሉ ዝግ፣ ጩኸቱ ሁሉ ሰሚ አልባ ሲመስለን፣ በመጨረሻ የምንወሰደው መፍትሔ ነገር ዓለሙን ሁሉ መተውና መሸነፍ ይሆናል፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ አበቃ›› ማለት እንጀምራለን፡፡ እንኳን እኛ ቀርቶ ሌሎች እንኳን እንዳይበረቱ ‹‹ባክህ እኛም ብለነው ብለነው አቅቶን ነው›› እያልን ተስፋ እናስቆርጣቸዋለን፡፡
ግን ሰው መልፋት ያለበት፣ መትጋትስ ያለበት፣ መታገልስ ያለበት፣ መሮጥስ ያለበት እስከ የት ነው? ሰው ተስፋ መቁረጥ ያለበት የት ደረጃ ሲደርስ ነው? የመንገድ ማለቂያው የት ነው? ውጤቱን ዛሬ ያላየነው ነገር ሁሉ ውጤት አልባ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላልን? በታሰበው ጊዜ ያልተደረሰበት ነገር ሁሉ ሊደረስበት የማይችል ነገር ነው ማለት ነው? መንገዱስ ይሄ እኛ የያዝነው መንገድ ብቻ ነውን? በሌላ መንገድስ ሊሞከር አይቻልምን?
መሆኑ ከማቆምና ከመቀጠል የትኛው ይመረጣል? ከማቆም ምን ይገኛል? ከተስፋ መቁረጥ በቀር፡፡ የሚጓዝ ሰው ጊዜው ይረዝም ይሆናል እንጂ አንድ ቀን የሚፈልገው ቦታ ይደርሳል፡፡ የቆመ ሰው ግን እንኳን ወደሚፈልግበት ለመሄድ ወደ ተነሣበት ቦታም ተመልሶ አይደርስም፡፡ የሚታገል ሰው አንድ ቀን ያሸንፋል፤ ያቆመ ሰው ግን ሳይማረክ እጁን ሰጥቷል፡፡ ደጋግሞ የሚያንኳኳ ሰው ከተኙት ሰዎች አንዱን መቀስቀሱ አይቀርም፤ ማንኳኳት ያቆመው ግን እንኳን ሊቀሰቅስ ራሱም ይተኛል፡፡ የሚሄድ መኪና ጋራጅ ይደርሳል፤ የቆመ መኪና ግን ባለበት ይወላልቃል፡፡
ለማሸነፍ ትልቁ መፍትሔ አቋምን መቀየር ሳይሆን መንገድን መቀየር ነው፡፡ የተለያዩ ነገሮችን መሞካከር ሳይሆን አንድን ነገር በተለያዩ መንገዶች መሞከር ነው፡፡ የተለያዩ ነገሮችን ማየት ሳይሆን አንድን ነገር በተለየ መንገድ ለማየት መቻል ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን፣ በውሳኔ ጊዜ መቁረጥ መቻል ነው፡፡ የምታገኘውን ሞት ከመመኘት የማታገኛትን ሕይወት በሚገባ ለመኖር ጣር፡፡
ሁለት ዕንቁራሪቶች እየተጓዙ ነበር፡፡ አንዷ ወፍራም ሌላዋም ቀጭን ነበሩ፡፡ እንዳጋጣሚ በገረወይና የተሞላ ወተት አገኙና ሰፍ ብለው ገቡበት፡፡ እዚያም አስኪበቃቸው ጠጡና ሲጠግቡ መውጣት ፈለጉ፡፡ ነገር ግን ውስጡ ያንዳልጥ ስለ ነበር ለመውጣት አልቻሉም፡፡ እግራቸውን ባንቀሳቀሱ ቁጥር ወተቱ እያንዳለጠ እዚያው ይጨምራቸዋል፡፡ ከጠዋት እስከ እኩለ ቀን ድረስ እጅግ ደከሙ፤ ነገር ግን ከድካም በቀር ያተረፉት ትርፍ አልነበረም፡፡
በምን ቀን ነው እዚህ ወተት ውስጥ የገባነው? እያሉ ቀናቸውን የሚያማርሩበት ሰዓት ላይ ደረሱ፡፡ የሚያማክሩት ሽማግሌ የሚጠይቁት ባለሞያ በአካባቢያቸው አልነበረም፡፡ ወደ ኋላ ተጉዘው የሰሟቸውንና ያዩዋቸውን ነገሮች ሁሉ አስታወሱ፡፡ ነገር ግን ለዚህ ነገር መፍትሔ የሚሆን ነገር ማስታወስ አልቻሉም፡፡ ወደ ሰማይ ቢጸልዩ እንኳን ጸሎታቸው የተሰማ አልመሰላቸውም፡፡ አንዳች ፈጣን መልስ አላገኙምና፡፡ በአካባቢው የሚያልፉ ሰዎችም ሆኑ ሌሎች ዕንቁራሪቶች ድምፃቸውን ሰምተው ከማለፍ በቀር ዘወር ብለው ሊያዋቸው አልቻሉም፡፡ አንዳንዶቹም ከገረወይናው ውስጥ የሚሰማው ዕንቁራሪቶች ድምፅ ከተለመደው ውጭ ነው ብለው ለማሰብ አልቻሉም፡፡
ወፍራሟ ዕንቁራሪት ተስፋ ቆረጠች፡፡ ‹‹በቃን፤ ከድካም በቀር የተረፈን የለም፡፡ ለመውጣት መታገሉን ማቆም አለብን›› አለች፡፡ ቀጭኗ ግን ‹‹ የለም ከተስፋ መቁረጥ የምናገኘው ምንም ነገር የለም፡፡ ተቀምጦ ከመሞት እየታገሉ መሞት፤ ተሸንፎ ከመሞት እያሸነፉ መሞት፤ እጅ ሰጥቶ ከመሞት እጅን እያሠሩ መሞት፣ አልችልም ብሎ ከመሞት እችላለሁ ብሎ መሞት የተሻለ ነውና አታቁሚ›› አለቻት፡፡
‹‹እስኪ ተመልከቺ ከጠዋት ጀምረን ለፋን፡፡ የጠጣነው ወተት እንኳን እስኪያልቅ ድረስ ለፋን፡፡ ከሰማይም ሆነ ከምድር የደረሰልን የለም፡፡ የእኛም ድካም ውጤት አላመጣም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የምናደርገው ሁሉ ቀልድ ይመስለኛል፡፡ ተንቦጫረቅን ተንቦጫረቅን፤ ወይ የሚንቦጫረቁ ልጆች የሚያገኙትን ደስታ አላገኘን፤ አለበለዚያም ደግሞ ከዚህ ቦታ መውጣት አልቻልንም፡፡ ታድያ የልፋታችን ዋጋው ምንድን ነው? እዚህ ቦታ መልፋታችንን እንኳን ያወቀልን የለም፡፡››
‹‹የሚረዳን ብናገኝ እንኳን የምንጠቀመው እኛ ለመውጣት የምንደርገውን ተጋድሎ ካላቋረጥን ብቻ ነው፡፡ ከልምድ መፍትሔውን የምናገኘው እኛ ጥረታችንን ካላቋረጥን ብቻ ነው፡፡ አንድ ቀን ይህንን ችግር ልናሸንፈው የምንችለው እኛ እየጣርን ከቀጠልን ብቻ ነው፡፡›› አለቻት ቀጭኗ ዕንቁራሪት፡፡
‹‹ባለፈው ጊዜ አታስታውሽም ቅቤ ውስጥ የገቡት ሦስት ዕንቁራሪቶች ምን ሆኑ?›› ወፍራሟ ይህንን ስትጠይቅ ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት እያቆመችው ነበር፡፡
‹‹ለምን የተሸነፉትን ትጠቅሻቸዋለሽ? ከተሸነፉት መማር ያለብንኮ ለምን ተሸነፉ የሚለውን እንጂ የጥረት መጨረሻው መሸነፍ መሆኑን አይደለም፡፡ ሽንፈትኮ ትምህርት አያስፈልገውም፡፡ ሽንፈትኮ ልምድ አያስፈልገውም፡፡ ዕውቀት አያስፈልገውም፡፡ ሽንፈት እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ብቻ ይበቃዋል፡፡ ለሽንፈት ምሳሌ መጥቀስ አያስፈል ግሽም፡፡ ሽንፈት ማለት በቀላሉ የሚደረስበት ነገር ነው፡፡ ሳትለፊ የምታገኚው ነገር ነው፡፡ ምሳሌ፣ አርአያ፣ ልምድ፣ ዕውቀት፣ ጥበብ፣ የሚያስፈልገው ድል ብቻ ነው፡፡ ስኬት ብቻ ነው፡፡ እርሱ በቀላሉ ስለማይገኝ ካገኙት ሰዎች ልምድና ጥበብ መቅሰም ያስፈልገዋል፡፡›› ቀጭኗ ዕንቁራሪት አሁንም በእግሮቿ ወተቱን መምታት አላቆመችም፡፡ እግሯ እየዛለ፤ ወገቧም እየከዳት ቢመጣም ግን ከወተቱ ላይ ተደግፋ ለመስፈንጠር በመታተር ላይ ነበረች፡፡
‹‹እሺ ይሄው አንቺ እስካሁን በመልፋት ላይ ነሽ፤ ግን ምን አመጣሽ? ቢያንስ ከድካሜ እፎይ ያልኩት እኔ አልሻልም››
‹‹ፈጽሞ አትሻይም›› አለቻት ቀጭኗ
‹‹እንዴት››
‹‹ቢያንስ እኔ ተስፋ አለኝ፤ አንቺ ግን የለሽም፡፡ እኔ በጥረት ውስጥ ደስታን አገኛለሁ፡፡ አንቺ ግን በኀዘን ውስጥ ነሽ፡፡ ጥረትኮ ባይሳካ እንኳን ደስታን ይሰጣል፡፡ ከቁዘማና ከድብርት ነፃ ያደርጋል፡፡ የሚጥር ስለነገ፤ ያቆመ ስለ ትናንት ያስባል፡፡ የሚጥር ስለ ኑሮ ያቆመ ግን ስለ ሞት ያስባል፡፡ በሩጫው ዓለም በመጀመርያዎቹ ዙሮች ቀዳሚውም መጨረሻውም እኩል ናቸው፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም ተሸናፊው ከአሸናፊው የተሻለ መስሎ የሚታይበትም ጊዜ አለ፡፡ ግን ደወል ይደወላል፤ ያን ጊዜም አሸናፊውና ተሸናፊው ይለያል፡፡››
‹‹በይ አንቺ እቴ አይሰለችሽም ቀጥይ፤ እኔ ግን በቃኝ፡፡ አንዳች ነገር ጠብ ላይል ምን አደከመኝ፡፡›› አለቻት ወፍራሟ ዕንቁራሪት፡፡
‹‹ቢያንስ ቢያንስ ደክሞሽ ሳታስቢው መሞት እየቻልሽ እንዴት ዓይንሽ እያየ ሰጥመሽ ትሞቻለሽ›› አለቻት ቀጭኗ፡፡
ወፍራሟ ግን አቆመች፡፡ ቀስ በቀስም ወደ ታች መስጠም ጀመረች፡፡ ቀጭኗ ዕንቁራሪት ልትረዳት ሞክራ ነበር፡፡ ነገር ግን ወፍራሟ ምንም ጥረት ስላላደረገች የርሷ ርዳታ ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ የሌላ እገዛ ውጤት የሚያመጣው የራስ ጥረት ካለ ብቻ ነው፡፡ አፉን ያልከፈተን ሰው ማጉረስ፣ ላልተፈተነም ሰው ቦነስ መስጠት አይቻልም፡፡
ወፍራሟ ዕንቁራሪት ቀስ በቀስ ወደ ወተቱ ዕቃ ሥር ገባችና ተሰናበተች፡፡
ቀጭኗ ግን አሁንም ጥረቷን አላቋረጠችም፡፡ በእግሯ አንዳች ለመቆንጠጥ እየሞከረች ትታገላለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ የወፍራሟ ጓደኛዋ መፍትሔ ይሻላል? እያለች ታስባለች፡፡ ግን ደግሞ የዚያችን መሞትና ቢያንስ የርሷን መኖር ስታየው እንደዚህ ማሰቧንም ትቃወመዋለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቆም ብላ ቀጥሎ ምን ሊመጣ እንደሚችል ታስባለች፡፡ ግን ምንም ነገር ታጣበታለች፡፡ ያን ጊዜ የምታደርገው ነገር ትክክል ይሁን ስሕተት ማረጋገጥ ትቸገራለች፡፡ በእርሷና በጓደኛዋ መካከል ያለውን ልዩነት የመሞቻ ጊዜ ልዩነት ይሆን? ብላም ታስባለች፡፡
እንዲህ እያሰበች እግርዋንም እያወናጨፈች ሌሊቱን በድካም አሳለፈችው፡፡ እናም ነጋ፡፡
ሲነጋም እንደዚሁ በእግሯ መወናጨፍን መስፈንጠርያ መፈለጉን ተያያዘችው፡፡ እኩለ ቀን ድረስ ግን ምንም አልነበረም፡፡
እኩለ ቀን ላይ እግሮቿን ስታወናጭፍ አንዳች ደረቅ ነገር ነካች፡፡ ልቧ በደስታ ቀጥ ሊል ነበር፡፡ ከየት ተገኘ? አለች፡፡ እንዴት እስከ ዛሬ አላገኘሁትም?
ለካስ ላለፉት ሰዓታት ወተቱን በእግሯ ስትመታው ወተቱ እይተናጠ፣ እየተናጠ፣ እየተናጠ ሄዷል፡፡ ከጊዜ በኋላም ወደ ቅቤነት ተቀይሯል፡፡ ያን ጊዜ እግሯ የሚረግጠው ነገር አገኘ፡፡ እርሱንም ተደግፋ ከገረወይናው ውስጥ ዘልላ ወጣች፡፡
‹‹ይብላኝ ተስፋ ቆርጦ ለሚያቆም እንጂ፣ የጣረስ አንዳች መውጫ ነገር ያገኛል›› አለች ምድር ስትደርስ፡፡

Comments

comments

Leave a Reply

Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>